ሕገ ሙሴ
From Wikipedia, the free encyclopedia
ሕገ ሙሴ በብሉይ ኪዳን ዘንድ ከአስርቱ ቃላት ቀጥሎ ከኦሪት ዘጸአት ፳፩ ጀምሮ የሚገኝ እግዚአብሔር በደብረ ሲና ለሙሴ የገለጸው ሕግ ነው።
የእስራኤል ልጆች በዘፈንና በወርቃማ ላም ጣኦት ከተገኙ በኋላ፣ ያህዌ የከበደ ሕግ ሰጣቸው። የሕዝቡ ዘር ለተነበዩ በረከቶች እንዲዘጋጅ፣ ለሙሴ ዘመን የተመጣጠነ ሕግ እንዲሆን፣ የሰው ልጆችን በመቸኰል ሳይሆን በመታገሥ ወደ ሥልጣኔ እንዲያስለምዳቸው፣ ከጎረቤቶቹ ከመስጴጦምያ አገሮች ሕግጋት የተሻሸሉ ብያኔዎች እንደ ወሰነ ሊታይ ይቻላል። ከሕገ ሙሴ (ምናልባት 1661 ዓክልበ. የተገለጠ) አስቀድሞ ከወጡት ሕገጋት በተለይ ተመሳሳይ ኹኔታዎች የቆጠሩት የኡር-ናሙ ሕግጋት (1983 ዓክልበ.)፣ የሊፒት-እሽታር ሕግጋት (1832 ዓክልበ.)፣ የኤሽኑና ሕግጋት (1775 ዓክልበ. ግድም) እና የሃሙራቢ ሕግጋት (1704 ዓክልበ.) ይታወቃሉ።
በታሪካዊ ልማዶች ዘንድ፣ የአክሱም መንግሥት ግማሽ ከ950 ዓክልበ. ግድም እስከ 317 ዓ.ም. ድረስ ደግሞ በሕገ ሙሴ ሥር ነበረች። እንዲሁም በአይሁድ መንግሥታት ለምሳሌ የስሜን መንግሥት (317-1619 ዓም) እና ኻዛሪያ (ከ732-1008 ዓም ግድም) ተገኘ።
በትንቢተ ሚክያስ 6:8 መሠረት በሕጉ በድምሩ አስፈላጊ የሆኑት ፫ ጽንሰ ሀሣቦች ፍርድ፣ ምኅረትና ትሕትና ናቸው።
ወደ ፊትም ከሕገ ሙሴ መሠረት ሕገ ወንጌልና በሕገ ወንጌል የተመሠረቱ ሕግጋት (ለምሳሌ እንደ ፍትሐ ነገሥት) ተደረጁ። በኢየሱስ ትምህርት፣ ከሁሉ ትልቁ ሕግ ኦሪት ዘዳግም ፮፡፭ «አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ» የሚለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ትልቁ ኦሪት ዘሌዋውያን ፲፱፡፲፰ «ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ» ነው። አለበለዚያ በሃዋርያት ሥራ ፲፭፡፳፱ ዘንድ፣ ከሕገ ሙሴ ለክርስቲያናት አጥብቀው መጠበቅ ያሉባቸው ደንቦች (ቅጣቶቹም ባይሆኑም) «ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደምም፣ ከተናቀም (ከመብላት)፣ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ» የሚሉት ናቸው። የተረፉት የአይሁዶች ሕግጋት ግን ለማጥናትና ለማወቅ ለብዙ ክርስቲያናት ቁም ነገሮች ናቸው።