የይሖዋ ምሥክሮች ሉዓላዊው ጌታ አንድ እርሱም ይሖዋ ነው ብለው የሚያምኑ ክርስቲያናዊ ሃይማኖት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ዘመናዊ እንቅስቃሴ የጀመሩት በ1870ዎቹ ዓመታት ነው። በመጀመሪያ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ ነበር። በ1931 ግን የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ስም ተቀበሉ። (ኢሳይያስ 43፡10)
አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ ይሰበሰባሉ። አብዛኞቹ ስብሰባዎች በይሖዋ ምስክሮች የስብሰባ አዳራሾች ውስጥ ይካሄዳሉ። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች በየዓመቱ ሦስት ትላልቅ ስብሰባዎች ያካሂዳሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኘው በኒው ዮርክ ነው።።
(1) መጽሐፍ ቅዱስ:- የይሖዋ ምሥክሮች ጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል ነው ብለው ያምናሉ፤ በሰው ወግ ላይ የተመሠረተን እምነት ከመከተል ይልቅ ለእምነቶቻቸው ሁሉ መመዘኛ የሚያደርጉት መጽሐፍ ቅዱስን ነው።
(2) አምላክ:- ይሖዋ ብቻ እውነተኛ አምላክ መሆኑን በማመን ያመልኩታል። ስለ እርሱና እርሱ ለሰው ልጆች ስላወጣቸው ፍቅራዊ ዓላማዎች ለሌሎች ሰዎች በግልጽ ይናገራሉ። ስለ ይሖዋ አምላክ ለሕዝብ የሚመሰክር ማንኛውም ሰው የአንድ ቡድን ይኸውም “የይሖዋ ምሥክሮች” አባል መሆኑ ይታወቃል።
(3) ኢየሱስ ክርስቶስ:- የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ ክርስቶስ አንደኛው የሥላሴ አካል ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚያንብቡት የአምላክ ልጅ፣ የአምላክ ፍጥረታት በኩር፤ ሰው ከመሆኑ በፊት ሕልውና የነበረው፤ ሕይወቱ ከሰማይ ወደ ድንግል ማርያም ማኅፀን የተዛወረ፤ መሥዋዕት የሆነው ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱ ለሚያምኑበት ሁሉ የዘላለም ሕይወት መዳን የሚያስገኝ እንደሆነና ከ1914 እ.ኤ.አ. ጀምሮ አምላክ በምድር ሁሉ ላይ በሰጠው ሥልጣን ንጉሥ ሆኖ እየገዛ እንዳለ ያምናሉ።
(4) የአምላክ መንግሥት:- የይሖዋ ምሥክሮች የሰው ልጆች ተስፋ የአምላክ መንግሥት ብቻ ናት ብለው ያምናሉ። ይህች መንግሥት እውን መስተዳድር ነች፤ ሁሉንም ሰብዓዊ መስተዳድሮች ጨምሮ የአሁኑን ክፉ የነገሮች ሥርዓት በቅርቡ በማጥፋት ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሥርዓት ታቋቁማለች።
(5) ሰማያዊ ሕይወት:- 144,000 በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ መንግሥቱ ተካፋዮች በመሆን አብረውት ነገሥታት ሆነው እንደሚገዙ ያምናሉ። “ጥሩ” የሆኑ ሰዎች በሙሉ የሚያገኙት ሽልማት ወደ ሰማይ መሄድ ነው ብለው አያምኑም።
(6) ምድር:- አምላክ ለምድር ያለው የመጀመሪያ ዓላማ እንደሚፈጸም፣ ምድር ይሖዋን በሚያመልኩ ሰዎች ከዳር እስከ ዳር እንደምትሞላ፣ እነዚህም ሰዎች ሰብዓዊ ፍጽምና አግኝተው ለዘላለም እየተደሰቱ መኖር እንደሚችሉ፣ ሙታንም እንኳ ሳይቀሩ ከእነዚህ በረከቶች ተካፋዮች ለመሆን ከሞት እንደሚነሡ ያምናሉ።
(7) ሞት:- ሙታን ፈጽሞ አንዳች ነገር እንደማያውቁ፤ በአንድ ዓይነት መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ በሥቃይ ወይም በደስታ ላይ እንዳልሆኑ፣ በአምላክ አእምሮ ውስጥ ከመታሰባቸው በቀር በሌላ መንገድ በሕይወት እንደሌሉ፤ በዚህም ምክንያት ወደ ፊት የሚኖራቸው ተስፋ የተመካው በትንሣኤ ላይ እንደሆነ ያምናሉ።
(8) የመጨረሻ ቀኖች:- ከ1914 ጀምሮ የምንኖረው በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ እንደሆነ፣ በ1914 የተፈጸሙትን ነገሮች የተመለከቱ አንዳንድ ሰዎች የአሁኑ ክፉ ዓለም ሲጠፋ እንደሚያዩ፣ ጽድቅ ወዳድ የሆኑት ግን ከጥፋቱ ተርፈው በጸዳች ምድር ላይ እንደሚኖሩ ያምናሉ።
(9) ከዓለም የተለዩ መሆን:- ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ተከታዮቹ ሲናገር “ከዓለም አይደሉም” እንዳለው የይሖዋ ምሥክሮችም የዚህ ዓለም ክፍል ላለመሆን ከልብ ይጥራሉ። ለሰው እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅር ያሳያሉ። በፖለቲካዊ ጉዳዮች አይሳተፉም ወይም በማንኛውም ብሔር ውስጥ በሚደረጉ ጦርነቶች ጣልቃ አይገቡም። ለቤተሰቦቻቸው የሚያስፈልጉትን ቁሳዊ ነገሮች ማቅረብ ቢኖርባቸውም ዓለም በጉጉት የሚያሳድዳቸውን ቁሳዊ ሀብቶች ማሳደድ፣ የግል ዝና ማግኘትና ከመጠን በላይ በተድላ መጠመድ አይፈልጉም።
(10) የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ማድረግ:- በቤት ውስጥ፣ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታና በጉባኤያቸው በየዕለቱ የአምላክን ቃል በሥራ ላይ ማዋል አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ። አንድ ሰው ባለፈው ጊዜ ይከተለው የነበረው አኗኗር ምንም ይሁን ምን የአምላክ ቃል የሚያወግዛቸውን ሥራዎች ከተወና አምላካዊ ምክርን በሥራ ላይ ካዋለ ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የይሖዋ ምሥክር ከሆነ በኋላ ማንም ሰው ምንዝር፣ ዝሙት፣ ግብረ ሰዶም እየፈጸመ፣ አደንዛዥ ዕፅ እየወሰደ፣ እየሰከረ፣ እየዋሸ ወይም እየሰረቀ እኖራለሁ ቢል ከድርጅቱ ይወገዳል።[1]
- አምላክ። እውነተኛና ሁሉን ቻይ የሆነውን ይሖዋ የተባለውን አንድ አምላክ እናመልካለን። (መዝሙር 83:18፤ ራእይ 4:11) ይሖዋ የአብርሃም፣ የሙሴ እና የኢየሱስ አምላክ ነው።—ዘፀአት 3:6፤ 32:11፤ ዮሐንስ 20:17
- መጽሐፍ ቅዱስ። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለሰው ልጆች በመንፈሱ አማካኝነት ያስጻፈው መልእክት እንደሆነ እናምናለን። (ዮሐንስ 17:17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) እምነታችን የተመሠረተው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆኑት በ66ቱም መጻሕፍት ላይ ነው፤ እነዚህ መጻሕፍት በተለምዶ “ብሉይ ኪዳን” እና “አዲስ ኪዳን” በመባል ይታወቃሉ። ፕሮፌሰር ጄሰን ቤዱን የይሖዋ ምሥክሮች “የሚያምኑበትም ሆነ የሚያደርጉት ነገር ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ያደርጋሉ እንጂ አንድን ነገር አስቀድመው ከወሰኑ በኋላ ያንን የሚደግፍ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማግኘት አይሞክሩም” በማለት ጽፈዋል።[2] ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ እንቀበላለን፤ ሆኖም ሁሉም ነገር ቃል በቃል መወሰድ አለበት የሚል እምነት የለንም። የተወሰኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የተጻፉት በዘይቤያዊ ወይም በምሳሌያዊ አነጋገር ስለሆነ ቃል በቃል መወሰድ እንደሌለባቸው እንገነዘባለን።
- ኢየሱስ። የኢየሱስን ትምህርትም ሆነ እሱ የተወውን ምሳሌ እንከተላለን፤ በተጨማሪም የአምላክ ልጅ እንዲሁም አዳኝ እንደሆነ በማመን እናከብረዋለን። (ማቴዎስ 20:28፤ የሐዋርያት ሥራ 5:31) በመሆኑም ክርስቲያን ተብለን እንጠራለን። (የሐዋርያት ሥራ 11:26) እንዲሁም ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ እንዳልሆነና ለሥላሴ ትምህርት መሠረት የሚሆን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ እንደሌለ ከመጽሐፍ ቅዱስ አውቀናል።—ዮሐንስ 14:28
- የአምላክ መንግሥት። የአምላክ መንግሥት እውን የሆነ መስተዳድር እንጂ በክርስቲያኖች ልብ ውስጥ ያለ ነገር አይደለም። ይህ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን የሚተካ ሲሆን አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ እንዲፈጸም ያደርጋል። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10) የአምላክ መንግሥት እነዚህን እርምጃዎች የሚወስደው በቅርቡ ነው፤ ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንደሚጠቁሙት የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ማቴዎስ 24:3-14 ኢየሱስ በሰማይ ያለው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ነው። መግዛት የጀመረው በ1914 ነው።—ራእይ 11:15
- መዳን። ሰዎች ከኃጢአትና ከሞት መዳን የሚችሉት በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ነው። (ማቴዎስ 20:28፤ የሐዋርያት ሥራ 4:12) አንድ ሰው ከዚህ መሥዋዕት ጥቅም ማግኘት ከፈለገ በኢየሱስ ማመን ብቻ ሳይሆን አኗኗሩን መለወጥና መጠመቅ ይኖርበታል። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ዮሐንስ 3:16፤ የሐዋርያት ሥራ 3:19, 20) አንድ ሰው የሚያደርገው ነገር እምነቱ ሕያው መሆን አለመሆኑን ያሳያል። (ያዕቆብ 2:24, 26) ይሁንና መዳን በሥራ ሳይሆን ‘በአምላክ ጸጋ’ የሚገኝ ነገር ነው።—ገላትያ 2:16, 21
- ሰማይ። ይሖዋ አምላክ፣ ኢየሱስ ክርስቶስና ታማኝ መላእክቱ የሚኖሩት በመንፈሳዊው ዓለም ማለትም በሰማይ ነው። * (መዝሙር 103:19-21፤ የሐዋርያት ሥራ 7:55) በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ጥቂት ቁጥር ያላቸው ማለትም 144,000 ሰዎች ከሞት ተነስተው በሰማይ ከኢየሱስ ጋር ይገዛሉ።—ዳንኤል 7:27፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:12፤ ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 3
- ምድር። አምላክ ምድርን የፈጠረው ለሰው ልጆች መኖሪያ እንድትሆን ነው። (መዝሙር 104:5፤ 115:16፤ መክብብ 1:4) አምላክ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ፍጹም ጤናና የዘላለም ሕይወት በመስጠት ይባርካቸዋል።—መዝሙር 37:11, 34
- ክፋትና መከራ። ክፋትና መከራ የጀመሩት ከአምላክ መላእክት አንዱ በማመፁ ነው። (ዮሐንስ 8:44) ይህ መልአክ ካመፀ በኋላ “ሰይጣን” እና “ዲያብሎስ” ተብሎ መጠራት የጀመረ ሲሆን የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት በዓመፅ ድርጊቱ እንዲተባበሩት አሳምኗቸዋል፤ ይህ ደግሞ በዘሮቻቸው ላይ አስከፊ መዘዝ አስከትሏል። (ዘፍጥረት 3:1-6፤ ሮም 5:12) ሰይጣን ላነሳው አከራካሪ ጉዳይ መልስ ለመስጠት አምላክ በምድር ላይ ክፋትና መከራ እንዲኖር ፈቅዷል፤ ሆኖም እነዚህ ነገሮች ለዘላለም እንዲቀጥሉ አይፈቅድም።
- ሞት። ሰዎች ሲሞቱ ከሕልውና ውጪ ይሆናሉ። (መዝሙር 146:4፤ መክብብ 9:5, 10) በእሳታማ ሲኦል አይሠቃዩም። አምላክ በትንሣኤ አማካኝነት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞት እንዲነሱ ያደርጋል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) ይሁንና ከሞት ከተነሱ በኋላ የአምላክን መንገድ ለመከተል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች ለዘላለም ይጠፋሉ፤ የትንሣኤ ተስፋም አይኖራቸውም።—ራእይ 20:14, 15
- ቤተሰብ። አምላክ የጋብቻ ዝግጅትን ያስጀመረው አንድን ወንድና ሴት በማጣመር ሲሆን እኛም ይህን በጥብቅ እንከተላለን፤ ለፍቺ ምክንያት የሚሆነው የፆታ ብልግና ብቻ እንደሆነ እናምናለን። (ማቴዎስ 19:4-9) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙት ጥበብ ያዘሉ ምክሮች የቤተሰብ ሕይወት ስኬታማ እንዲሆን እንደሚረዱ እናምናለን።—ኤፌሶን 5:22 እስከ 6:1
- አምልኳቸው። መስቀልን ወይም ሌሎች ምስሎችን ለአምልኮ አይጠቀሙም። (ዘዳግም 4:15-19፤ 1 ዮሐንስ 5:21) በአምልኳቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሚሰጧቸው ነገሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
- ለአምላክ መጸለይ።—ፊልጵስዩስ 4:6
- መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ማጥናት።—መዝሙር 1:1-3
- ከመጽሐፍ ቅዱስ በተማርነው ነገር ላይ ማሰላሰል።—መዝሙር 77:12
- ለጸሎት፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት፣ ለመዘመር፣ እምነታችንን ለመግለጽና የእምነት ባልንጀሮቻችንንም ሆነ ሌሎችን ለማበረታታት መሰብሰብ።—ቆላስይስ 3:16፤ ዕብራውያን 10:23-25
- ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ መስበክ።—ማቴዎስ 24:14
- ችግር ላይ የወደቁትን መርዳት።—ያዕቆብ 2:14-17
- የመንግሥት አዳራሾችን እንዲሁም ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ ለማስፋፋት የሚያገለግሉ ሌሎች ሕንጻዎችን መገንባትና መጠገን።—መዝሙር 127:1
- በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱ ሰዎችን መርዳት።—የሐዋርያት ሥራ 11:27-30
- ድርጅታችን። በጉባኤዎች የተደራጀን ሲሆን እያንዳንዱን ጉባኤ በበላይነት የሚከታተለው የሽማግሌዎች አካል ነው። ሆኖም ሽማግሌዎች የቀሳውስት ቡድን አይደሉም፤ እንዲሁም ደሞዝ አይከፈላቸውም። (ማቴዎስ 10:8፤ 23:8) አስራት አንጠይቅም፤ በስብሰባዎቻችን ላይም ገንዘብ አይሰበሰብም። (2 ቆሮንቶስ 9:7) ለምናደርጋቸው ሥራዎች የገንዘብ ድጋፍ የምናገኘው ስማቸው የማይገለጽ ለጋሾች ከሚያደርጉት መዋጮ ነው። በዋናው መሥሪያ ቤት የሚያገለግለው የበላይ አካል በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች አመራር ይሰጣል፤ የበላይ አካሉ አባላት ጥቂት ቁጥር ያላቸው የጎለመሱ ክርስቲያኖች ናቸው።—ማቴዎስ 24:45
- አንድነታችን። እምነታችን በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ አድርጎናል። (1 ቆሮንቶስ 1:10) በተጨማሪም በመካከላችን በኑሮ ደረጃ፣ በጎሣ፣ በዘር ወይም በመደብ ክፍፍል እንዳይኖር ጥረት እናደርጋለን። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35፤ ያዕቆብ 2:4) አንድነት አለን ሲባል የግል ምርጫና አመለካከት የለንም ማለት አይደለም። እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ሕሊናው ተጠቅሞ የራሱን ውሳኔ ያደርጋል።—ሮም 14:1-4፤ ዕብራውያን 5:14
- ምግባራችን። በምናደርገው ነገር ሁሉ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን። (ዮሐንስ 13:34, 35) ደም እንደ መውሰድ ካሉ አምላክን ከሚያሳዝኑ ድርጊቶች እንርቃለን። (የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29፤ ገላትያ 5:19-21) ከሰዎች ጋር በሰላም የምንኖር ሲሆን በጦርነትም አንካፈልም። (ማቴዎስ 5:9፤ ኢሳይያስ 2:4) የምንኖርበትን አገር መንግሥት የምናከብር ሲሆን ከአምላክ ሕግ ጋር እስካልተጋጨ ድረስ የዚያን አገር ሕጎች እንታዘዛለን።—ማቴዎስ 22:21፤ የሐዋርያት ሥራ 5:29
- ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት። ኢየሱስ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷል። እንዲሁም ክርስቲያኖች “የዓለም ክፍል አይደሉም” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 22:39፤ ዮሐንስ 17:16) በመሆኑም ‘ለሁሉም ሰዎች መልካም ብናደርግም’ ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሙሉ በሙሉ ገለልተኛ ነን፤ ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ኅብረት ከመፍጠርም እንርቃለን። (ገላትያ 6:10፤ 2 ቆሮንቶስ 6:14) ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ ሌሎች የሚያደርጉትን ውሳኔ እናከብራለን።—ሮም 14:12[3]
ትሩዝ ኢን ትራንስሌሽን የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 165