ክሮኖስ
From Wikipedia, the free encyclopedia
ክሮኖስ በጥንታዊ ግሪክ አፈ ታሪክ በኩል የአረመኔ እምነት አማልክት ኡራኖስና ጋያ ልጆች የሆኑት የቲታኖች መሪ የነበረ አምላክ ወይም ንጉሥ ነበረ። አባቱን ገልብጦ በአፈታሪካዊ ወርቃማ ዘመን ይነግሥ ነበር፤ በኋላ ግን የራሱ ልጆች ዚውስ፣ ሃይዴስና ፖሠይዶን ክሮኖስን ገለበጡ፣ በታርታሮስም አሠሩት።
የክሮኖስ ስም በሮማይስጥ «ሳቱርን» ሲሆን በነርሱም እምነት እንደ አምላክ ይቆጠር ነበር። የፈልኩ ሳተርን ስም እንዲሁም የቅዳሜ ዕለት ስም (ሳተርደይ) በእንግሊዝኛ ከርሱ የተወሰደ ነው።
የግሪክ ጸሐፊ ሄሲዮድ እንዳለው፣ ክሮኖስ አባቱን ኡራኑስን በመቀኝነት ያየው ነበር፤ እናቱም ጋያ በኡራኑስ ላይ ጠላትነት አገኘች። ስለዚህ ጋያ ክሮኖስን ማጨዳ ሠጠችውና ክሮኖስ አባቱን ሰለበው። ዳሩ ግን ሌሎች ታላላቅ ልጆች («ጊጋንቴስ») ከተፈሰሰው ደም ተወለዱ።
ከዚሁ በኋላ ክሮኖስ ዕኅቱን ሬያን አገባትና ንጉሥና ንግሥት ሆነው ዓለሙን ገዙ። ይህም «ወርቃማ ዘመን» የተባለው ነበር፤ እያንዳንዱ ግለሠብ በምግባር ስለ ሠራ ለድንጋጌዎች አስፈላጊነት ያልነበረበት ወቅት መሆኑ ታመነ።
ክሮኖስና ሬያ ብዙ ሌሎች አማላክት ወለዱ፦ ዴሜቴር፣ ሄራ፣ ሃይዴስ፣ ሄስቲያ እና ፖሠይዶን ነበሩ። ዳሩ ግን ክሮኖስ በገዛው ልጆች እንዲገለበጥ ስለሚል ትንቢት፣ እያንዳንዱ እንደ ተወለደ እርሱ በላቸው። ስለዚህ ስድስተኛው ልጅ ዚውስ ሲወለድ እናቱ በስውር ቦታ በክሬታ ደሴት እንዲታደግ አደረገች። ከታደገ በኋላ ዚውስ መድኃኒት ለክሮኖስ አጠጣውና ወንድሞቹን እንዲያውካቸው አስደረገው። ዚውስ፣ ወንድሞቹና ጊጋንቴስ ከክሮኖስ ኃያላት ጋር ቲታኖማኬ የተባለ አፈታሪካዊ ጦርነት ተዋጉ። ከዚሁ ጦርነት በኋላ ክሮኖስ በታርታሮስ ታሠረ። በፒንዳር ዕትም ግን ክሮኖስ ከዚያ በኋላ ወጣና የኤሊሲዩም ንጉሥ ሆነ። ዊርጊል ደግሞ እንደጻፈው፣ ሳቱርን (ክሮኖስ) ከዚያ ወጥቶ የላቲዩም (በጣልያን) ንጉስ ሆነ።
በጣልያን አፈ ታሪክ ረገድ ደግሞ የክሮኖስ ወይም የስቱርን ስም አንዳንዴ ከ«ካሜሲስ» ወይም ከ«ካሜሴኑስ» ስም ጋር ይለዋወጣል። ለምሳሌ አኒዩስ ዳ ቪቴርቦ ባሳተመው ዜና መዋዕል ውስጥ፣ «ሳቱርን» እንደ ማዕረግ ሲቆጠር፣ መጀመርያውም «የባቢሎን ሳቱርን» ናምሩድ ሲባል፣ የኖኅ ልጅ ካም (ወይም ካሜሴኑስ) «የግብጻውያን ሳቱርን» ሆኖ ከዚያ በሊብያ፣ በጣልያንና በባክትሪያ በተራ ይገዛል፤ ከሃሞን፣ ከቲታኖችና በኋላም ከኒንያስ ጋር ይዋጋል።