From Wikipedia, the free encyclopedia
የ2019-20 ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከባድ እና አጣዳፊ የመተንፈሻ አካላት በሽታ አምጪ በሆነው SARS-CoV-2 ቫይረስ ምክንያት የተከሰተ የኮሮናቫይረስ በሽታ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ነው። ወረርሽኙ ለመጀመርያ ጊዜ የተገኘው በቻይና ዉሃን ሁቤ ውስጥ በእ.ኤ.አ. ዲሴምበር 2019 ነበር። የዓለም ጤና ድርጅት በእ.ኤ.አ. ማርች 11 ቀን 2020 በሽታውን የወረርሽኝ ደረጃ ላይ መድረሱን አወጀ። እስከ መጋቢት እ.ኤ.አ. ማርች 29 ቀን 2020 ድረስ ባለው መረጃ መሠረት ከ670 ሺህ በላይ የኮቪድ-19 ኬዞች በ199 አገራት ውስጥ ተመዝግበዋል። በበሽታው 31,191 ሰዎች ሲሞቱ ወደ 143,840 ገደማ የሚሆኑት ደግሞ አገግመዋል። በወረርሽኙ በዋነኝነት ከተጠቁት አገራት መካከል ቻይና ፣ ኢጣልያ ፣ ኢራን ፣ ደቡብ ኮርያ እና ስፔን ይገኙበታል።
ልክ እንደ ኢንፍሉዌንዛ የቫይረሱ ዋነኛ መተላለፊያ መንገድ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ሲያስሉ ወይም ሲያስነጥሱ ከሚረጩ ፈሳሾች ነው። በሽታው ተላላፊ ነው ተብሎ የሚወሰደው ሰዎች የበሽታውን ምልክቶች በሚያሳዩበት ወቅት ቢሆንም አንድ አንድ ጊዜ ምልክቱን የማያሳዩ ሰዎች በሽታውን ሊያስተላልፉ ይችላሉ። አንድ ሰው ለቫይረሱ ከተጋለጠ በኋላ በአማካይ በአምስት ቀን ውስጥ ምልክቶችን ማሳየት ይጀምራል። ነገር ግን ምልክቱ እስኪታይ እስከ ዐሥራ አራት ቀን የሚቆይበት ሁኔታ አለ። የተለመዱት ምልክቶቹ ትኩሳት ፣ ሳል እና የትንፋሽ መቆራረጥ ናቸው። በሽታው ሲባባስ የሣንባ ምች እና የተለያዩ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎችን ሊያስከትል ይችላል። በአሁኑ ጊዜ በሽታው ክትባት ወይም የጸረ-ቫይረስ ህክምና የለውም። በሽታውን ለመከላከል እጅን መታጠብ ፣ ሲያስሉ እና ሲያስነጥሱ አፍን መሸፈን ፣ በሽታው ካለባቸው ሰዎች ራቅ ማለት እናም በሽታው ካለባቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት ከነበረ ራስን ለ14 ቀናት ማግለል ይመከራል።
የበሽታውን መስፋፋት ለመቀነስ የጉዞ ዕገዳዎችን መጣል ፣ ለይቶ ማቆያዎችን ማዘጋጀት ፣ ሠዓት እላፊን መጣል ፣ የተለያዩ ሕዝባዊ ዝግጅቶችን መሠረዝ ወይም ማስተላለፍ እና ብዙ ሰዎች የሚገኙባቸውን ተቋሞችን መዝጋት በዓለም ላይ ከተወሰዱት እርምጃዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።
ይህ ወረርሽኝ ዓለምአቀፋዊ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን አስከትሏል። የተለያዩ የባሕላዊ እና የስፖርታዊ ዝግጅቶችም ተሠረዘዋል። በመድሃኒት ፣ ኤሌክትሮኒክስ እና ምግብ ረገድ የአቅርቦት እጥረት ይፈጠራል የሚል ፍርሃትንም በሰዎች ውስጥ አሳድሯል። በዚህም ምክንያት በምዕራቡ ዓለም ሰዎች ዕቃዎችን በማግበስበስ እንደ መጸዳጃ ቤት ወረቀት ያሉ መሠረታዊ ዕቃዎች ላይ ከፍተኛ ዕጥረት እንዲፈጠር አድርገዋል።
ምልክት[3] | % |
---|---|
ትኩሳት | 87.9% |
ደረቅ ሳል | 67.7% |
ድካም | 38.1% |
አክታ | 33.4% |
ትንፋሽ ማጠር | 18.6% |
የጡንቻ ወይም የመገጣጠምያ ህመም | 14.8% |
የጉሮሮ ህመም | 13.9% |
ራስ ምታት | 13.6% |
ብርድ ብርድ ማለት | 11.4% |
ማቅለሽለሽ ወይም ማስመለስ | 5.0% |
የአፍንጫ መደፈን | 4.8% |
ተቅማጥ | 3.7% |
ደም ማሳል | 0.9% |
የዓይን መቅላት እና ማበጥ | 0.8% |
በኮቪድ-19 የተጠቁ ሰዎች አንዳንዴ ምንም ምልክት ላያሳዩ ሲችሉ የተቀሩት ደግሞ እንደ ኢንፍሉዊንዛ ዓይነት ምልክቶች የሆኑትን እንደ ድካም ፣ ሳል ፣ ትኩሳት ፣ የትንፋሽ ማጠር እና የጡንቻ ህመሞች ይታዩባቸዋል። የተለመዱት የበሽታ ምልክቶች በቀጣዩ ሰንጠረዥ ውስጥ ተካትተዋል።
በሽታው ሲከፋ ከባድ የሣንባ ምች ፣ የተለያዩ አጣዳፊ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ፣ ከባድ ኢንፌክሽኖችን እንዲሁም ሞትን ሊያስከትል ይችላል። አንዳንድ በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ምንም ምልክት ሳያሳዩ ግን በላቦራቶሪ ምርመራ በሽታው ሊገኝባቸው ይችላል። በዚህም ምክንያት ከነዚህ ሰዎች ጋር ቅርብ ንክኪ የነበራቸው ሰዎች የቅርብ ክትትል እንዲደረግላቸው ተመራማሪዎች ይመክራሉ።
የበሽታው ምልክት የመታየት ጊዜ አብዛኛውን ጊዜ አምስት ቀን ቢሆንም ከአንድ ቀን እስከ ዐሥራ አራት ቀን ሊሆንም ይችላል። በአንድ ኬዝ እስከ 27 ቀን የቆየበት ሁኔታም ታይቷል።[4]
የቫይረሱ ቀዳሚ የመተላለፊያ መንገድ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ሲያስሉ ወይም ሲያስነጥሱ ከሚረጩ ፈሳሾች ነው። ፈሳሾቹ ዓየር ላይ ለትንሽ ጊዜ ቢሆንም የሚቆዩት እንደ ብረት ፣ ካርቶን ፣ መስታወት እና ፕላስቲክ ዕቃዎች ላይ ረዘም ላለ ጊዜ ሊቆዩ ይችላሉ። ቫይረሱ ልክ እንደሌሎች ኮሮናቫይረሶች ዓየር ላይ እና አንዳንድ ቁሳቁሶች ላይ እስከ ዘጠኝ ቀን ሊቆይ የሚችልበት ሁኔታዎች አሉ።[5]
Seamless Wikipedia browsing. On steroids.
Every time you click a link to Wikipedia, Wiktionary or Wikiquote in your browser's search results, it will show the modern Wikiwand interface.
Wikiwand extension is a five stars, simple, with minimum permission required to keep your browsing private, safe and transparent.