1 እሽመ-ዳጋን
From Wikipedia, the free encyclopedia
1 እሽመ-ዳጋን ከ1688 እስከ 1678 ዓክልበ. ('ኡልትራ አጭሩ' አቆጣጠር[1]) የአሦር ንጉሥ ነበረ። አባቱ 1 ሻምሺ-አዳድ የአሦር ንጉሥ እየሆነ፣ ልጁን እስመ-ዳጋንን በኤካላቱም ዙፋን ላይ አስቀምጦት ነበር። ታናሹ ወንድሙ ያስማሕ-አዳድ ደግሞ የማሪን ዙፋን ተቀበለው። በባቢሎን ንጉሥ ሃሙራቢ 17ኛው አመት (በ1688 ዓክልበ.) 1 ሻምሺ-አዳድ እንደ ሞቱ ልጁም እሽመ-ዳጋን የአሦርን መንግሥት እንደ ወረሰው ይታወቃል።
በዘመኑ መጀመርያ፣ የሑራውያን ቱሩኩ ጎሣ አለቃ ሊዳይ ጽኑ አመጽ በሹሻራ አገር አስነሣሣ። ክፍላገሩ በተለይ ተራራማ ስለ ሆነ፣ እሽመ-ዳጋን የአሦርን ሠራዊት ሹሻራን እንዲተው አደረገ። ከዚያ ግን ኡታን አገር አሸነፈ። በተሸነፈው አገር በኡታ ሥልጣኑን ለመጠብቅ፣ ወንድሙን ያስማሕ-አዳድ ከማሪ ወደ ኡታ እንደራሴነት አዛወረው። በስደት የኖረው የማሪ ቀድሞ ንጉስ ዚምሪ-ሊም በዚያ ዕድሉን አገኝቶ ማሪን ከያስማሕ-አዳድ ነጥቆ ወደ ዙፋኑ ተመለሰ።
በእሽመ-ዳጋን ዘመን፣ አሦር ከማሪ፣ ከኤሽኑና እና ከኤላም ጋራ ጦርነት ያደርግ ነበር። ስለዚህ እሽመ-ዳጋን ከበፊቱ ጠላቶች ከቱሩኩ ሕዝብ ጋር የስምምነት ውል አደረገ። የቱሩኩ አለቃ ዛዚያ ሴት ልጅ ለእሽመ-ዳጋን ወንድ ልጅ ለሙት-አሽኩር ታጨች። በዚህ ወቅት ደግሞ የባቢሎን ሃይል እየበረታ አሦር ከባቢሎን ወዳጅነት ተጠቀመ። ሆኖም እሽመ-ዳጋን የአባቱን ግዛት በሙሉ ሊጠብቅ አልተቻለውም። በመጨረሻ ግዛቱ የኤካላቱም፣ አሹርና ነነዌ ከተሞች ዙሪያ ብቻ ያጠቅልል ነበር።
በማሪ ጽሑፎች እንደሚዘገብ፣ በዚምሪ-ሊም 9ኛው አመት (በ1679 ዓክልበ.)፣ ኤላማውያን እሽመ-ዳጋንን ከአገሩ አባረሩትና ወደ ባቢሎን ሸሸ። በዚያ በጽናት ታመመ። እሽመ-ዳጋን ማዕረጉን በይፋ ቢጠብቅም የሃሙራቢን ሥልጣን እንዲቀብል ተገደደ። በዝምሪ-ሊም 11ኛው አመት እሽመ-ዳጋን ዙፋኑን ለልጁ ለሙት-አሽኩር እንደ ተወው ይታወቃል። ሙት-አሽኩር ይቅርና ብዙ ሌሎች ሰዎች ዙፋኑን ለመያዝ ሞከሩ። ከነዚህም አሹር-ዱጉል አገሩን ለጥቂት አመት እንዲገዛ በቃ።