ጣና ሐይቅ (ቀደምት ባሕረ ጎጃም) በጎጃም ክፍለሃገር ውስጥ ሲገኝ ቅዱሱ ሐይቅም ይባላል።ጣና ሃይቅ በጥንታዊ ቋንቋ (ግእዝ) አገላለጽ ‹‹ጻና ሐይቅ›› ይባላል፡፡ድንግል ማርያም በገዳሙ የነበራትን ቆይታ አጠናቃ ስትመለስ “ፀአና በደመና” በደመና ጫናት የተባለው በጊዜ ብዛት ለአሁኑ የሐይቁ መጠሪያ ስም “ጣና” መሠረት ሆኖታል ነው የሚባለው።በክርስቶስ ልደት ገደማ ስለግብጽ ብዙ ምርምር ያደረገው ስትራቦ ዓባይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኝ ትልቅ ሐይቅ እንደሚነሳ ያውቅ ነበር ይባላል፡፡ የሐይቁን ስምም ስትራቦ “ሴቦ” ብሎታል፡፡
የሁለተኛው ዘመን የግብጽ መልክዓ ምድር ተመራማሪ ገላውዲዮስ ፕቶሎሚ ደግሞ “ኮሎ” ይለዋል፡፡
የአቴናው ድራማ ጸሐፊ አስክለስ “መዳብ የተቀባው ሐይቅ የኢትዮጵያ ጌጥ” ብሎታል፡፡ ባለቅኔው ሆሜርም “ከሌሎች የተለየና ጥርት ያለ የውኃ ባለቤት ነው” ብሎ ጠርቶታል፡፡ ከኢትዮጵያ አንደኛ እና ትልቁ ሐይቅ ነው። 84 ከ.ሜ. ረጅም እና 66 ኪ.ሜ. ሰፊ ነው። ባጠቃላይ 3,500 ካሬ ኪ.ሜ. ይሸፍናል።
ጣና በአጠቃላይ በውስጡ ከ37 በላይ ደሴቶች ሲኖሩት 27 ገዳማትን አቅፎ ይዟል።ገዳማቶች በ14ኛ ምእት ዓመት አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ባመነኮሷቸው ‹‹ሰባቱ ከዋክብት›› ተብለው በሚጠሩት ቅዱሳን አባቶች የተመሠረቱ ናቸው።ከገዳማቶች
መካከል፦
•••ደብረ ማርያም
•••ክብራን ገብርኤል
•••ዑራ ኪዳነምህረት
•••መሀል ዘጌ ጊዮርጊስ
•••አቡነ በትረ ማርያም
•••አዝዋ ማርያም
•••ዳጋ ኢስጢፋኖስ
•••ይጋንዳ ተለሃይማኖት
•••ናርጋ ስላሴ
•••ደብረ ሲና ማርያም
•••ማንድባ መድኃኒዓለም
•••ጣና ቂርቆስ
•••ክርስቶስ ሳምራ ገዳም
•••ራማ መድሕኒ ዓለም
•••ኮታ ማርያም…እና ሌሎችም ገዳማቶች ይገኙበታል።
•••
ሰባቱ ከዋክብት የሚባሉት አኩስም አቅራቢያ የሚገኘው የደብረ በንኮል ገዳም መሥራች አቡነ መድኅነ እግዚእ ደቀ መዛሙርት ናቸው።እነርሱም፦
1.አቡነ ታዴዎስ~ደብረ ማርያም መሥራች
2.አቡነ ዘዮሐንስ~የክብራን እና የእንጦስ ገዳም መሥራች
3. አቡነ በትረማርያም~የዘጌ ጊዮርጊስ መሥራች
4. አቡነ ኂሩተ አምላክ~የዳጋ እስጢፋኖስ መሥራች
5.አቡነ ኢሳይ~የመንዳባ መድኃኔዓለም መሥራች
6.አቡነ ዘካርያስ~ደብረ ገሊላ መሥራች
7.አቡነ ፍቁረዮሐንስ~ጣና ቂርቆስ መሥራች ናቸው።