የዔድን ገነት
From Wikipedia, the free encyclopedia
የዔድን ገነት (ዕብራይስጥ፦ גַּן עֵדֶן /ገን ዐድን/) በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት እግዚአብሔር በሰው ልጅ መጀመርያ ቅድመ ታሪክ በምድር የተከለ ገነት ነበረ። ይህ ገነት በተለይ የሚገለጸው በኦሪት ዘፍጥረት 2 እና 3፣ እንዲሁም በመጽሐፈ ኩፋሌ 4 እና 5 ነው፤ ደግሞ በትንቢተ ሕዝቅያስ 28 ይጠቀሳል። አንዳንዴ በመሳሳት «ዔድን» ሳይሆን የ«ኤዶም» ገነት ተብሏል፤ ኤዶም ግን በትክክል የያዕቆብ ወንድም ዔሳው የመሠረተው ሀገር ነበረ።
መጽሐፈ ኩፋሌ 4:14, 16 እንደሚያብራራልን፣ መጀመርዮቹ ሰዎች አዳም እና ሔዋን በገነት የቆዩበት ዘመን ሰባት አመታት ያህል ነበር። በመጽሐፈ ኩፋሌ አቆጣጠር አስርቱ ቃላት እስከ ተሰጡበት ዓመት ድረስ 2410 ዓመታት ስለሚቆጠር፣ እነዚህ ቅድመ ታሪካዊ ሰባት አመታት ከ4071 እስከ 4064 ዓክልበ. ያህል እንደ ነበሩ መረዳት ይቻላል። ሌሎች ግን በሌሎች ዘዴዎች በኩል ሌሎችን ፍቾች አገኝተዋል። አዳም ከተፈጠረበት ከሥነ-ፍጥረት 6ኛው ቀን ጀምሮ በአዳም 40ኛው ቀን ወደ ገነት እንደ ገባ፣ ሚስቱም ሔዋን በ80ኛው ቀን እንደ ገባች ይለናል (4:9, 12)። ወደ ገነትም ሳይገቡ በተወለዱበት አገር በኤልዳ እየቆየ አዳም መጀመርያው ሳምንት እንስሶችን ያሰይማቸው ነበር፣ ከ፪ኛውም ሳምንት ጀምሮ ሔዋንን ያውቃት ነበር። አዳም ከተፈጠረበት ከዓለም 6ኛው «ቀን» አስቀድሞ ዓለሙ፣ ምድሩ፣ አትክልቱና እንስሶች ሁሉ ወዘተ. ተፈጥረው ነበር፤ እነዚህ 6ቱ «ቀኖች» ግን እንደ አሁን የ24 ሰዓት ቀኖች እንደ ነበሩ አይመስልም።
በሥነ ቅርስ መጀመርያው የምናውቀው ታሪካዊ ሰነድ «የመንደሮቹ መኳያ ሰሌዳ» 3125-3100 ዓክልበ.ግ. ይመስላል፤ ከዚያ አስቀድሞ ለነበረው ዘመን የሰው ልጅ ታሪካዊ መዝገቦች (ሰነዶች) በፍጹም ባለመኖራቸው፣ ይህ ስለ «ቅድመ ታሪክ» አንድ ቅድመ-ታሪካዊ አስተያየት ሲሆን፣ በሰፊ በአብርሃማዊ ሃይማኖቶች (በተለይ ክርስትና፣ እስልምና፣ አይሁድና) የሚገኝ አስተያየት ነው። (ደግሞ ባለሙያ ንድፍን ይዩ።)
በዚሁም አጭር የገነት ወቅት ከአሁን በጣም የተለዩ ሁናቴዎች እንደ ነበሩ የሚል አሣብ ይፈጠራል።
- አዳም እና ሔዋን በኤድን ሲቆዩ መዋቲ መሆናቸው እንደ ታሠበ አይመስልም። ሞት ለሰው ልጆች የመጣበት ምክንያት አዳም እና ሔዋን በዓመፃ ጸባይ የተከለከለውን ፍሬ ተመግበው ከዔድን ገነት ስለ ተሰደዱ እንደ ሆነ ይመስላል።
- የእንስሶች ጉዳይ በግልጽ ባይብራራልንም ከአዳም ጋር ለመናገር በዚሁ ወቅት ችሎታው እንደ ነበራቸው በኩፋሌ 5:2 ይጻፋል።
- እባብ በዚህ ሰዓት እግሮቹን ገና ስላላጣ ባለ እግር ፍጡር እንደ ነበር ይመስላል።
- የእግዚአብሔር መላእክት ለአዳምና ሔዋን የገነት አጠባበቅ በነዚህ 7 አመቶች ያስተምራቸው ነበር (ኩፋሌ 4:14)።