አቡነ ቴዎፍሎስ
From Wikipedia, the free encyclopedia
አቡነ ቴዌፍሎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁለተኛው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ ጎጃም በሚገኝው በዝነኛው ደብረ ኤሊያስ አካባቢ ከአባታቸው ከአቶ ወልደ ማርያም ውቤ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ዘርትሁን አደላሁ ሚያዝያ ፲፮ ቀን ፲፱፻፪ ዓ/ም ተወለዱ። ሲወለዱም የተሰጣቸው ስም መልእክቱ ወልደ ማርያም ነበር።
በልጅነታቸው ንባብ እና ዜማን በመምህር መሪ ጌታ ረዳኸኝ እና ግራ ጌታ ሣህሉ እዚያው የተወለዱበት አካባቢ ተምረዋል። ኋላ የቅኔ እና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ዝንባሌ ስላደረባቸው እዚያው ደብረ ኤሊያስ ደብር መምህር ገብረ ሥላሴ በሚባሉ ሊቅ ሥር መማር ጀመሩ።
በ፲፱፻፻፳ ዓ/ም ወደ አዲስ አበባ መጥተው ፍትሐ ነገሥትና አዲስ ኪዳንን በመምህር ተክሌ (ነቡረ ዕድ በኋላ ቢትወደድ አቡነ ዮሐንስ) በመባል የሚታወቁት መሪነት ሲከታተሉ ቆይተዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ የኃይማኖት ችግሮችን ለማወቅ ይፈልጉ እንደነበርና ሰፋ ያለ ዕውቀት እንደነበራቸው ይነገራል። በተጨማሪ የኃይማኖት ችግሮችን የሚመለከቱ መጻሕፍትን ሳይታክቱና ሳይሰለቹ ያነቡም ነበር።
መልእክቱ ወልደ ማርያም በ፲፱፻፴ ዓ/ም ይህን ዓለም በቃኝ ብለው ደብረ ሊባኖስ ገዳም መንኩሰው ገቡ። ከጠላት ወረራ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቀሳውስቱ በዘመናዊ የኃይማኖት ትምህርት እንዲሠለጥኑ በነበራቸው ሀሳብ መሠረት ፳ የሚሆኑ ሊቃውንት መርጠው በቤተ መንግሥቱ አካባቢ እንዲሰለጥኑ አድርገዋል። ከነኚህም አንዱ አባ መልእክቱ ወልደ ማርያም ናቸው።
ቀደም ብሎ በኢትዮጵያና በግብጽ በተደረገው ስምምነት መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያዊያን ጳጳሶች ሲሾሙ ሊቀ ሥልጣናት መልእክቱ ወልደ ማርያም ለሹመት ከተመረጡት አምስት አባቶች አንዱ ሲሆኑ ወደግብጽ ተጉዘው በእስክንድርያው ፓትርያርክ ዳግማዊ አቡነ ዮሳብ እጅ በካይሮ በትረ ካና ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን እሑድ ሐምሌ ፲፰ ቀን ፲፱፻፵ ዓ/ም ሊቀ ሥልጣናት መልእክቱ “ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ” ተብለው የሐረርጌ ጳጳስ ሆኑ።