From Wikipedia, the free encyclopedia
ርብቃ (ዕብራይስጥ፦ רִבְקָה /ሪብቃህ/) በኦሪት ዘፍጥረት መሠረት የይስሐቅ ሚስትና የያዕቆብና የኤሳው እናት ነበረች። በምዕራፍ ፳፪፡፳፫ አባቷ ባቱኤል ነበር። (ባቱኤልም የአብርሃም ወንድም ናኮርና የሚልካ ልጅ ነበር።)
ምዕራፍ ፳፬ እንደሚተርክ፣ አብርሃም ሽማግሌ ሆኖ ልጁም ይስሐቅ የከነዓን ሴት እንዳያገባ ከዘመዶቹ ሚስት ያገኝለት ዘንድ ሎሌውን ወደ «መስጴጦምያ» (ዕብራይስጥ፦ አራም-ናሓራይን) ላከው። ሎሌው ግመሎችን ይዞ ወደ አብርሃም ወንድም ናኮር ከተማ ደረሰ። ናኮር የኖረው በአራም አገር ቢሆን ትውልዱ እንደ ወንድሙ አብርሃም ከአርፋክስድ ዘር ነበር። የሎሌው ስም ባይሰጥም በ፩ ጥንታዊ ልማድ በምዕራፍ ፲፭፡፪ የተጠቀሰው ሎሌ የደማስቆ ሰው ኤሊዔዘር ነበረ።
ሎሌው ግመሎቹን በውኃ ምንጭ አጠገብ አስቀመጣቸውና ግመሎቼን ያጠጣችው እርስዋ የጌታዬ ልጅ እጮኛ ትሁን የሚል ጸሎት ጸለየ። ወዲያው ርብቃ መጥታ ግመሎቹን አጠጣች። ሎሌው የወርቅ ቀለበትና አምባር ሰጣት። ነገሩን ለቤተሠብዋ ከገለጸላቸው በኋላ፣ አባቷ ባቱኤልና ወንድሟ ላባ ፈቃዳቸውን ሰጡ። ርብቃና ሎሌው አብረው ወደ ከነዓን በግመል ተመልሰው እርስዋና ይስሐቅ ተያይተው ተዋደዱና ተዳሩ።
በምዕራፍ ፳፭ ርብቃ ለይስሐቅ መንታ ልጆች እነርሱም ያዕቆብንና ኤሳውን እንደ ወለደችለት ይነግራል። በምዕራፍ ፳፮ ዘንድ ይስሐቅ በጌራራ ቆይቶ ንጉሣቸውን አቢሜሌክ ርብቃ እህቴ ነች አላት። (በዘፍጥረት ፳ ስለ አቢሜሌክ፣ አብርሃምና ሣራ ተመሳሳይ ታሪክ አለ፣ በመጽሐፈ ኩፋሌ ግን አቢሜሌክ ከይስሐቅና ርብቃ ጋር የነበረው መዋዋል ብቻ ይጠቀሳል፤ እንዲሁም አብርሃምና ሣራ ከግብጽ ፈርዖን ጋር ተመሳሳይ ጉዳይ ነበራቸው።) በኋላ በዘፍጥረት ፳፯ ርብቃ ልጇን ያዕቆብ የኤሳውን በረከት ከይስሐቅ እንዲቀበል መከረችው።
Seamless Wikipedia browsing. On steroids.
Every time you click a link to Wikipedia, Wiktionary or Wikiquote in your browser's search results, it will show the modern Wikiwand interface.
Wikiwand extension is a five stars, simple, with minimum permission required to keep your browsing private, safe and transparent.