ፉጥ
From Wikipedia, the free encyclopedia
ፉጥ (ደግሞ ፉድ በኩፋሌ፤ ዕብራይስጥ፦ פוט /ፉጥ/ ግሪክ፦ Φουδ /ፉድ/) በኦሪት ዘፍጥረት ምዕ. 10 መሠረት የካም ልጅ ነው።
የጥንት ሊቃውንት «ፉጥ» ጥንታዊ ሊብያውያን («ለቡ» እና «ፒቱ») እንደ ነበሩ በማለት ይስማማሉ። እነዚህ ነገዶች የግብጽ ጎረቤቶች በስተ ምዕራብ ተገኙ። ዮሴፉስ እንደ ጻፈው፦ «ፉጥ ደግሞ የሊቢያ መስራች ነበረ፣ ከራሱም ኗሪዎቹን፦ «ፉጣውያን» አላቸው፤ ደግሞ በሞሮች አገር በዚያው ስም የሚሰየም ወንዝ አለ፤ ስለዚህ ነው አብዛኞቹ ግሪክ የታሪክ ጸሐፍት ያንን ወንዝና ዙሪያውን «ፉጥ» በሚል ስያሜ የሚጠቅሱት፤ ነገር ግን አሁን ያለው ስም በለውጥ ከምጽራይም ልጅ ከሊብዮስ ተሰጠው።» ይህም 'ፉጥ ወንዝ' በፕሊኒና በፕቶሎሜዎስ መጻሕፍት ዘንድ በዛሬው ሞሮኮ ይገኝ ነበር። ፕቶሎሜዎስ ደግሞ «ፑቴያ» የተባለች ከተማ በልብያ እንዳለች ይጠቅሳል።
በብሉይ ኪዳን ትንቢተ ናሆም 3፡9 እንዲሁም «ፉጥና ሉቢም» (ልብያ) የግብጽ ረዳቶች ይባላሉ። በሌሎች መጻሕፍት ደግሞ የፉጥ ልጆች ጦረኞች ይላቸውዋል። በትንቢተ ኤርምያስ 46፡9 እንደገና የግብጽ ረዳቶች ይላቸዋል። ትንቢተ ሕዝቅኤል ሦስት ጊዜ ይጠቅሳቸዋል፦ በ27፡10 የጢሮስ (ፊንቄ) ረዳቶች፣ በ30፡5 የግብጽ ረዳቶች፣ በ38፡5 የጎግ ረዳቶች ናቸው። በዕብራይስጥ «ፉጥ» ሲለው በሕዝቅኤል ግሪኩ ትርጉም (ከ300 ዓክልበ.) «ሊቡዌስ» ይላል። በትንቢተ እሳይያስ 66፡19 ሩቅ አገር ይባላል።
የፋርስ ታሪክ ጸሐፊ ሙሐመድ እብን ጃሪር አል-ታባሪ (907 ዓ.ም. ገደማ) በጻፈው ልማድ ዘንድ፣ የፉጥ ሚሥት ስም ባኅት ሲሆን እስዋ የቲራስ ልጅ የባታዊል ልጅ ነበረችና 'ቅብጦቹን' ወለደችለት።
የጥንታዊ ግብጽ መንግሥት ሰነዶች ወደ ፑንት ሀገር ስለተደረጉት ጉዞዎች ሲጽፉ፣ ይህ ቦታ ግን ሊብያ ሳይሆን በቀይ ባሕር ዳር እንደ ተገኘ ይመስላል። ሆኖም በአንዳንድ ዘመናዊ አስተሳሰብ ዘንድ ፑንት ከፉጥ ጋር ግንኙነት እንዳለው ይታስባል።
ፒዱ ወይም ፒቱ የተባለ የልብያ ነገድ በምሥር መዝገቦች በ900 ዓክልበ. ይታያል። በኋላ በቅብጥኛ ቋንቋ ልብያ «ፋያጥ» ይባል ነበር።
የናቡከደነጾር ዜና መዋዕል በ575 ዓክልበ. በግብጽ ባደረገው ዘመቻ በ«ፑቱ ያዋን» (ኩሬኔ) ሠራዊት ላይ እንዳሸነፈ ይጠቅሳል። በዳርዮስ ዘመን፣ «ፑቲያ» (በፋርስኛ) ወይም «ፑጣ» (በአካድኛ) የተባለ ክፍላገር በሊብያ ነበረ።
Wikiwand in your browser!
Seamless Wikipedia browsing. On steroids.
Every time you click a link to Wikipedia, Wiktionary or Wikiquote in your browser's search results, it will show the modern Wikiwand interface.
Wikiwand extension is a five stars, simple, with minimum permission required to keep your browsing private, safe and transparent.