From Wikipedia, the free encyclopedia
ዓፄ ፋሲለደስ ወይም ዓፄ ፋሲል (የዙፋን ስማቸው ዓለም ሰገድ) ከአባታቸው አፄ ሱሰኒዮስ እና ከእናታቸው ልዕልት ስልጣነ ሞገስ በሸዋ ክፍለሀገር ቡልጋ መገዘዝ ፣ ህዳር 10፣ 1603 (እ.ኤ.አ) ተወለዱ። የነገሱበትም ዘመን ከ1632 እስከ ጥቅምት 18, 1667 (እ.ኤ.አ) ነበር።
==
ዓፄ ፋሲለደስ | |
---|---|
የፋሲል ምስል፣ ኡራ ኪዳነ ምህረት | |
ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ | |
ግዛት | ከ1632 እስከ 1667 እ.ኤ.አ. |
ቀዳሚ | ዓፄ ሱስንዮስ |
ተከታይ | ቀዳማዊ ዓፄ ዮሐንስ |
ሙሉ ስም | ዓለም ሰገድ (የዙፋን ስም) |
ሥርወ-መንግሥት | ሰሎሞን |
አባት | ዓፄ ሱስንዮስ |
እናት | እቴጌ ስልጣን ሞገስ |
የተወለዱት | 1603 እ.ኤ.አ. |
የሞቱት | 1667 እ.ኤ.አ. በአዘዞ |
የተቀበሩት | ቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም፤ ደጋ ደሴት |
ሀይማኖት | የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና |
==
በስረፀ ክርስቶስ በተመራው አመፅ ምክንያት በ1630 ፋሲለደስ ለንግስና ቢበቃም፣ ዘውዱን ግን እስከ 1632 አልጫነም ነበር። ሲመተ ንግስናው በ1632 እንደተገባደደ የመጀመሪያው ስራው የተዋህዶ ቤ/ክርስቲያንን የቀድሞው ቁመና መመለስና የካቶሊኮችን መሬት በመቀማት ከደንካዝ በማባረር በፍሪሞና እንዲወሰኑ ማድረግ ነበር። ወዲያውም በማከታተል ከግብፅ አገር አዲስ ጳጳስ እንዲላክለት በማድረግ በአባቱ ዘመን እንዲደበዝዝ ተደርጎ የነበረውን የግብፅና ኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት እንዲጸና አደረገ። በኬኒያ የሚገኘው የሞምባሳ ወደብ በፖርቱጋሎች መደብደቡን ሲሰማ፣ የሮማው ፓፓ ከበስትጀርባው ያለበት ሴራ ነው በማለት በምድሩ የነበሩትን የካቶሊክ ጀስዊቶች በመሰብሰብ አባረራቸው።
ፋሲለደስ የጎንደር ከተማን በ1636 የኢትዮጵያም ዋና ከተማ አድርጎ እንደቆረቆራት ይታመናል።[1] ከሱ በፊት በአካባቢው ከተማ እንደነበር ወይም እንዳልነበር በታሪክ የተገኘ ማስርጃ እስካሁን የለም። አከታትሎም የፋሲል ግቢንና 44ቱ ታቦታት ተብለው የሚታወቁትን የጎንደር ከተማ አብያተ ክርስቲያናት መሰረት ጣለ። በአፄ ፋሲል ከተመሰረቱት ታዋቂወቹ 44 አብያተ ክርስቲያናት፣ ታዋቂወቹ አደባባይ እየሱስ፣ አደባባይ ተክለ ሃይማኖት፣ አጣጣሚ ሚካኤል፣ ግምጃቤት ማራያም፣ ፊት ሚካኤል፣ እና ፊት አቦ ይገኙበታል።[2] ያለመታከትም 7 የድንጋይ ድልድዮችን በማሰራት እስካሁን ድረስ ስሙ ሲጠራ ይኖራል። አልፎም በግራኝ አህመድ ዘመን በእሳት ጋይቶ የነበረችውን አክሱም ፂዮን በአዲስ መሰረት እንደገና ማሰራት ችሎአል።[3]
ፋሲለደስ በዘመኑ እጅግ ተወዳጅ ንጉስ ቢሆንም አመጽ መነሳቱ አልቀረም። በላስታ ለምሳሌ በ1637 መልክዓ ክርስቶስ በተባለ ሰው መሪነት ጦርነት ተነስቶ አፄ ፋሲልን ስጋት ላይ ቢጥልም በሚቀጥለው አመት በተደረገው ጦርነት አመፁ ሊገታ ችሎአል።[4]
ፋሲለደስ ፖርቱጋሎችን ቢያባርርም ከውጭው አለም ጋር ብዙ ግንኙነት ያደርግ ነበር። ለምሳሌ በ1664-5 የህንድ ንጉስ አውራንግዘብ ሲነግስ መልካም ምኞትን በመልክተኞቹ ለሙግሃሉ መሪ ልኮ ነበር።
በ1666 ልጁ ዳዊት ሲያምጽ፣ ወህኒ ተብሎ ወደሚታወቀው አገር በግዞት ልኮት ነበር። ይህም ከጥንቶቹ የኢትዮጵያውን ነገሥት ተፎካካሪያቸውን ወደ አምባ ግሽን በግዞት እንደሚልኩት ስርዓት ነበር።
አፄ ፋሲል አዘዞ ተብላ በምትታወቀው ከጎንደር ከተማ 5 ማይል ርቃ በምትገኘው ከተማ ጥቅምት18፣1667 እ.ኤ.አ. (ጥቅምት 10፣ 1660) ከዚህ አለም በሞት ተለዩ። አሟሟታቸውንም፣ በጊዜው በህዝቡ ዘንድ የነበራቸውን ተቀባይነት በሚያንጸባርቅ መልኩ፣ የዜና መዋዕል ዘጋቢያቸው እንዲህ ሲል ይተርካል፡
አስከሬናቸውም የአገሪቱ መላ ህዝብ ባዘነበት ሁኔታ በቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም፣ ጣና ሃይቅ ውስጥ ደጋ ደሴት ተብላ በምትታወቀው ደሴት የዘላለም እረፍት አገኘ። መቃብራቸውም ውስጥ ያንድ ትንሽ ህፃን አስክሬን አብሮ ይገኛል። ይሄውም ልጃቸው ሲሆን የወደፊቱ ንጉስ ለመሆን እጩ ነበር። ነገር ግን አዲሱን ንጉስ የመጣው ህዝብ ብዛት ሲተራመስ ድንገት ተጠቅጥቆ ለሞት በቃ።[6]
Seamless Wikipedia browsing. On steroids.
Every time you click a link to Wikipedia, Wiktionary or Wikiquote in your browser's search results, it will show the modern Wikiwand interface.
Wikiwand extension is a five stars, simple, with minimum permission required to keep your browsing private, safe and transparent.