ጋያነሸጎዋ
From Wikipedia, the free encyclopedia
ጋያነሸጎዋ ወይም ካያነረኮዋ («ታላቅ ሕገ ሰላም») የሆደነሾኒ (ኢሮኳ) ኗሪ ብሔሮች የተባበሩበት ሕገ መንግሥት ነው። በተለመደው ታሪክ ዘንድ፣ በ1100 ዓ.ም. ገደማ አለቃው ደጋናዊዳ በዛሬው ኒው ዮርክ ክፍላገር የሚኖሩትን 5 ብሔሮች በዚህ ሕግ አባበራቸው። 5ቱ ብሔሮችም በስም ካንየንከሃካ (ሞሃውክ)፣ ኦንዮታአካ (ኦናይዳ)፣ ኦኖኝዳጌጋ (ኦኖንዳጋ)፣ ጋዮጎሆኖ (ካዩጋ)፣ እና ኦኖንዶዋጋ (ሰነካ) ናቸው። በኋላም በ1706 ዓ.ም. ስድስተኛ ብሔር ተስከሮራ ተጨመረላቸው።
የአሜሪካ ኗሪዎች ኅብረተሠብ እንደ አውሮፓውያን ኅብረተሠብ ፊዎዳል አገዛዝ ሳይሆን ዴሞክራስያዊ (ሕዝባዊ) ነበረ። ስለዚህ ይህ ሕግ በ1780 ዓ.ም. በተደረገው በአሜሪካ ሕገ መንግሥት ላይ ሰፊ ተጽእኖ ነበረው። ለዚህም የሚቀርበው ታሪካዊ ሰነድ የላንካስተር ውል (1738 ዓም) ነው።
ይህ ሕግ የተመዘገበው በተጻፈ ቋንቋ ሳይሆን በዋምፖም (ትንንሽ የዛጎል ዶቃዎች) አማካይነት ይታወስና ይወረስ ነበር። በኋላ ዘመን ነው ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመ። ሕጉ በ117 አንቀጾች ይከፈላል። የተባበሩት ሆደነሾኒ ብሔሮች የጥድ ዛፍ ምሳሌ ናቸው። እያንዳንዱ ጎሣ ወይም ነገድ በመንግሥት አመራር የተወሰነ ሚና ያጫውታል።