ቀጭኔ በአፍሪካ የሚኖር ባለሙሉ ጣት ሸሆኔ ጡት አጥቢ አራዊት ሲሆን በምድር ከሚገኙ እንሰሳት በርዝማኔ የመጀመሪያውን ደረጃ ይዞ ይገኛል። ወንዱ ከ 4.4 እስከ 5.5 ሜትር ርዝማኔና 1,360 ኪሎግራም ክብደት ያስመዘግባል። እስካሁን በሪኮርድ የተያዘው የ 5.87ሜና የ2000ኪ.ግ ቀጭኔ ነው።[2] ሴቶቹ በጥቁቱ አነስ ብለው ይታያሉ።

More information ?ቀጭኔ, የአያያዝ ደረጃ ...
?ቀጭኔ
Thumb
የአያያዝ ደረጃ
Thumb
በአጠባበቅ ልድን የቻለ (LR/cd)[1]
ሳይንሳዊ ደረጃ መስጫ
ስፍን: ጉንደ እንስሳ (Animalia)
ክፍለስፍን: አምደስጌ (Chordata)
መደብ: አጥቢ (Mammalia)
ክፍለመደብ: ሙሉ ጣት ሸሆኔ Artiodactyla
አስተኔ: የቀጭኔ አስተኔ Giraffidae
ወገን: ቀጭኔ Giraffa
ዝርያ: G. camelopardalis
ክሌስም ስያሜ
''Giraffa camelopardalis''
Linnaeus, 1758
Thumb
Close

ፈጣንና ባለ ግርማ

እነዚህን ፍጥረታት በአራዊት ማቆያ ቦታዎች አንገታቸውን ከታጠሩበት አጥር በላይ ወጣ አድርገው የተመለከተ ሰው በአፍሪካ ቁጥቋጦዎች ነፃ ሆነው ሲሮጡ ያላቸውን ውበትና ግርማ መገመት ያስቸግራል። የቀጭኔ እንቅስቃሴ ትልቅ ግርማ ያለውና እንደ ውኃ ሙላት የሚፈስ ነው። በገላጣው የግጦሽ መስክ ላይ በሚጋልቡበት ጊዜ ቁመናቸው ትንሽ እንቅፋት ቢነካቸው ወድቀው የሚሰባበሩ ያስመስላቸዋል። ይሁን እንጂ እስከ 1, 300 ኪሎ ግራም የሚደርስ ክብደት ያላቸው ወንድ ቀጭኔዎች ቀልጣፋና ምንም የማያደናቅፋቸው ሯጭ ከመሆናቸውም በላይ በሰዓት እስከ 60 ኪሎ ሜትር ሊሮጡ ይችላሉ።

ይህች አስደናቂ ፍጡር የምትገኘው በአፍሪካ ብቻ ነው። እርጋታዋና ሰላማዊ ተፈጥሮዋ ዓይን ይስባል። የቀጭኔ ፊት በዓይነቱ ልዩ የሆነና ቆንጆ ሊባል የሚችል ሲሆን ረዥምና ጠባብ ጆሮዎች፣ ሁለት ትናንሽ ቀንዶች እንዲሁም ጠቆር ያለ ለስላሳ ጠጉር አላት። ዓይኖቿ በጣም ትላልቅና ጥቁር ሲሆኑ ረዣዥም በሆኑ ቅንድቦች ይጠበቃሉ። ቀጭኔ ያን በመሰለ ከፍታ ላይ ሆና ሩቅ ስትመለከት ፊቷ ላይ የየዋህነት ገጽታ ይታይባታል።

በጥንት ዘመናት ቀጭኔ ባላት አስደሳች ቁመና እንዲሁም ጨዋ፣ ዓይነ አፋርና ሰላማዊ ባሕርይ ያላት በመሆኑ በጣም ተወዳጅና ትልቅ ግምት የሚሰጣት ነበረች። በብሔራት መካከል ሰላምና በጎ ፈቃድ መኖሩን ለማመልከት የቀጭኔ ግልገሎች ለነገሥታትና ለገዥዎች በገጸ በረከትነት ይሰጡ ነበር። ጥንታዊ በሆኑት የአፍሪካ አለቶች ላይ ቀለማቸው የደበዘዘ የቀጭኔ ሥዕሎች እስከ ዛሬ ይታያል። [3]

ቁመተ ረዥም

ከእንስሳት ሁሉ ቀጭኔን በቁመት የሚወዳደር የለም። ሙሉ ዕድሜ ላይ የደረሱ ወንድ ቀጭኔዎች ከእግራቸው ኮቴ አንስቶ እስከ ቀንዳቸው ድረስ ከ5.5 ሜትር የሚበልጥ ርዝመት አላቸው። በግብፃውያን ጥንታዊ ሥዕላዊ የአጻጻፍ ዘዴ ቀጭኔ በረዥም ቁመቷና አርቆ በመመልከት ችሎታዋ ምክንያት “መተንበይ” የሚለውን ግሥ ትወክል ነበር።

ቀጭኔ በአፍሪካ መስኮች በሚሰማሩት የሜዳ አህዮች፣ ሰጎኖች፣ አጋዘኖችና ሌሎች እንስሳት መካከል ስትቆም እንደ ማማ ሆና ትታያለች። ቁመቷና አርቆ የማየት ችሎታዋ ማንኛውንም አደጋ ገና ከሩቅ ለማወቅ ያስችላታል። ስለዚህ የቀጭኔ መኖር ለሌሎች እንስሳት የመረጋጋት ስሜት እንደሚፈጥር ጥርጥር የለውም። [4]

አስደናቂ የሆነ አፈጣጠር

ቀጭኔ ከዝሆን በስተቀር ማንኛውም ሌላ እንስሳ ሊደርስ በማይችልበት ከፍታ ላይ የሚገኙ ረዣዥም ቀንበጠቦችን ለመብላት የሚያስችል አስደናቂ አፈጣጠር አላት። ልዩ የሆነ የመቆንጠጥ ችሎታ ያለው የላይኛው ከንፈሯና እንደተፈገለው የሚተጣጠፍ ችሎታ ያለው ምላሷ ሹል በሆኑ እሾሆች የታጠሩ ቅጠሎችን ለመቀንጠብ ያስችሏታል።

ቀጭኔዎች በቀን እስከ 34 ኪሎ ግራም የሚመዝን ዕፅዋት መመገብ ይችላሉ። የተለያዩ ዕፅዋትን የሚበሉ ቢሆኑም ይበልጥ የሚመርጡት በአፍሪካ ሜዳዎች የሚገኙትን እሾሃማ ግራሮች ነው። አንድ ወንድ ቀጭኔ ምግብ ለመፈለግ ምላሱን እስከ 42 ሳንቲ ሜትር መዘርጋት ይችላል። የቀጭኔ አንገት በጣም አስደናቂ የሆነ የመተጣጠፍ ችሎታ አለው። ይህም ላይኛዎቹን የዛፍ ቅርንጫፎች ለመቀንጠብ በምታደርገው እንቅስቃሴ ረዥሙን ራሷን እንደ ልቧ ለማዘንበልና ለማዟዟር ያስችላታል።

ለቀጭኔ ወደ ላይ መንጠራራት በጣም ቀላል ነገር ሲሆን ተጎንብሶ ውኃ መጠጣት ግን ይከብዳታል። ወደ ውኃ ጉድጓድ በምትቀርብበት ጊዜ የፊት እግሮቿን ቀስ በቀስ ከፍታ ካራራቀቻቸው በኋላ ወደ ውኃው ለመድረስ እንድትችል ሁለት ጉልበቶቿን አጠፍ ታደርጋለች። ቀጭኔዋ እንዲህ ባለው አመቺ ባልሆነ ሁኔታ እያለች ረዥም አንገቷን እስከ መጨረሻ ትዘረጋለች። ደግነቱ ግን ከምትመገባቸው ቅጠላ ቅጠሎች በቂ እርጥበት ስለምታገኝ ቶሎ ቶሎ መጠጣት አያስፈልጋትም።

የቀጭኔ አንገትና ትከሻ የቅጠል ቅርፅ ባላቸውና ቀጫጭን በሆኑ ነጭ መስመሮች ያጌጠ ነው። ቀለማቸው የተለያየ ሲሆን ከወርቃማ ዳለቻ አንስቶ እስከ ቡናማ እንዲያውም ጠቆር እስካለ ቀለም ይደርሳል። የቀጭኔ ዕድሜ እየገፋ በሄደ መጠን ቀለሟም እየጠቆረ ይሄዳል። [5]

የቤተሰብ ሕይወት

ቀጭኔዎች ከ2 እስከ 50 የሚደርሱ አባላት ባሉት መንጋዎች ተደራጅተው አንድ ላይ የሚኖሩ ማኅበራዊ ፍጥረታት ናቸው። አንዲት ነፍሰ ጡር ቀጭኔ ልጅዋን ከ420 እስከ 468 ለሚደርሱ እርግዝና ቀናት ከተሸከመች በኋላ ሁለት ሜትር ቁመት ያለው ግልገል ትወልዳለች። ግልገሏ በምትወለድበት ጊዜ ራስዋን ታስቀድምና ከሁለት ሜትር ከፍታ ላይ ወደ መሬት ትወረወራለች። ይሁን እንጂ በ15 ደቂቃ ውስጥ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባት እየተውተረተረች ትነሳና ጡት ለመጥባት ዝግጁ ትሆናለች። ከሁለት ወይም ከሦስት ሳምንት በኋላ በደመ ነፍስ ተመርታ የግራር ቀንበጦችን መለቃቀም ስለምትጀምር ብዙም ሳትቆይ ረዥም እርምጃ ያላትን እናትዋን ተከትላ ለመሄድ የሚያስችል ጉልበት ታገኛለች።

አንዲት የቀጭኔ ግልገል በጣም ውብ መልክ ሲኖራት የወላጆችዋ አነስተኛ ግልባጭ ነች። ቁመቷ ከቀጭኔ ርዝመት ጋር ሲወዳደር አጭር ብትሆንም ከብዙ ሰዎች ቁመት ግን ትበልጣለች። በእናቷ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥበቃ ተማምና አላንዳች መሸበር አካባቢዋን የምትማትረው ግልገል ላያት ሁሉ ልዩ መስህብ አላት።

ግልገል ቀጭኔዎች በተወለዱበት ወራት በግልገል መዋያ ተሰባስበው ሙሉውን ቀን ዕረፍት በማድረግ፣ በመጫወትና በአካባቢያቸው የሚሆነውን ነገር በመመልከት ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ። የቀጭኔ ግልገል ለማመን በሚያዳግት ፍጥነት ያድ⁠ጋል። በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ አንድ ሜትር የሚያክል ቁመት ሲጨምር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ደግሞ በእጥፍ ያድጋል። በአንድ ሳምንት ብቻ 23 ሳንቲ ሜትር ያህል ሊያድግ ይችላል! እናትዬው ለልጅዋ ከፍተኛ ጥበቃ የምታደርግ ሲሆን ልጅዋ የተወሰነ ርቀት እንድትዘዋወር ብትፈቅድላትም ሩቅ የማየት ችሎታ ስላላት በዓይኗ ትከታተላታለች።

ቀጭኔ ግዙፍ አካል፣ ከፍተኛ ፍጥነት፣ ቅልጥፍናና የማየት ችሎታ ስላላት ከአንበሳ በቀር የሚያጠቃት ጠላት የለም። ቢሆንም ይህችን የምታምር ፍጥረት የሰውን ያህል በብዛት አድኖ የገደለ የለም። ቀጭኔ በሚያምር ቆዳዋ፣ በሚጣፍጥ ሥጋዋና አንዳንዶች ምትሐታዊ ኃይል አለው በሚሉት ረዥምና ጥቁር ጭራዋ ምክንያት እጅግ ተፈላጊ ስለሆነች በአሁኑ ጊዜ የዚህች ሰላማዊ ፍጡር የወደፊት ሕልውና ስጋት ላይ ወድቋል። በአንድ ወቅት በብዙ የአፍሪካ አካባቢዎች እንደ ልብ ትታይ የነበረችው ቀጭኔ በአሁኑ ጊዜ የምትገኘው በቂ ጥበቃ በሚደረግላት ፓርኮች ብቻ ሆኗል። [6]

[የግርጌ ማስታወሻ]

በአፍሪካ ገላጣ ምድር ላይ በሰፊው ተሰራጭተው የሚታዩት ትናንሽ ዓለታማ ኮረብቶች ኮፕጀስ ይባላሉ።

Wikiwand in your browser!

Seamless Wikipedia browsing. On steroids.

Every time you click a link to Wikipedia, Wiktionary or Wikiquote in your browser's search results, it will show the modern Wikiwand interface.

Wikiwand extension is a five stars, simple, with minimum permission required to keep your browsing private, safe and transparent.