From Wikipedia, the free encyclopedia
ሰንጠረዥ (ወይም ቼዝ) በዓለም ዙሪያ የተወደደ ጥንታዊ የገበታ ጫዋታ ነው።
ስለ ሠንጠረዥ መጀመርያ በአብዛኛው የታሪክ ሊቃውንት የተቀበለው ሀልዮ በሕንድ አገር ከ500 ዓ.ም. ግድም አስቀድሞ እንደ ተለመደ የሚለው ነው። ሆኖም ከዚያ በፊት ግሪኮች በታላቁ እስክንድር ዘመን ወደ ሕንድ እንዳስገቡት የሚያስቡ ደራስያን ኖረዋል። በዚህ ሀሣብ በትሮያን ጦርነት ወቅት (1200 አክልበ. ያሕል) በፓላሜዴስ ተፈጠረ። እንኳን ከግሪኮች በፊት የእስኩቴስ ሰዎች እንዳወቁት የሚል አስተሳሰብ ደግሞ ሊገኝ ይቻላል።
በሕንድ አገር በድሮ 2 ተመሳሳይ ቻቱራንጋ የተባሉት ጨዋታዎች ነበሩ፦ እነርሱም ባለ 4 እጅ ቻቱራንጋ እና ባለ 2 እጅ ቻቱራንጋ ናቸው። «ቻቱራንጋ» የሚለው ቃል በሳንስክሪት ቋንቋ ከ«ቻቱር» (አራት) ማለት 'አራት መደቦች' ነው።
ባለ 4 እጅ ቻቱራንጋ ላይ፣ አራት ሠራዊት በአራት ሰዎች ይታዘዛሉ። እያንዳንዱ ተጫዋች 1 ንጉስ፣ 1 ዝሆን (ግንብ)፣ 1 ፈረስ፣ 1 መርከብ (ጳጳስ) እና 4 ወታደር ይቀበላል። መርከቡም በማዕዘን ጀምሮ ሁለት ቦታ ብቻ በሰያፍ ይዘልላል። ይህ ጨዋታ ከጥንት በዛህራ ይጫወት ነበር። ቁማር ግን ጽድቅ እንዳልተቆጠረበት መጠን ያለ ምንም ዛህራ ደግሞ ተጫውቷል። በአንዳንድ ደራሲ አስተሳሰብ ዘንድ፣ ይህ አይነት ቻቱራንጋ በቀዳሚ የታወቀው ነው። ነገር ግን በጽሑፍ ዘንድ የመኖሩ ማስረጃ ከ1000 ዓ.ም. ብቻ ስለሚገኝ፣ የዛሬ ታሪክ ሊቃውንት ይህን አሳብ አይቀበሉም።
ባለ 2 እጅ ቻቱራንጋ በጽሁፍ የሚታወቅ ከ500 ዓ.ም. ገዳማ ነው። በዚህ አይነት 2 ሠራዊቶች አሉ። እንደ ዛሬ ቼዝ እያንዳንዱ ሠራዊት 2 ግንቦች፣ ፈረሶችና ጳጳሳት፤ 8ም ወታደሮች አሉት። በንግሥት ፋንታ ግን 'አማካሪ' (ጠቅላይ ሚኒስትር) የሚባል ክፍል አለ። ይህ ክፍል ደካም ነው፤ 1 ቦታ በሰያፍ ብቻ ይሄዳል።
ከሕንድ አገር ጨዋታው በ550 ዓ.ም. ወደ ፋርስ መንግሥት እንደ ገባ የሚሉ ታሪኮች አሉ። በፋርስኛ የሳንስክሪት ስም «ቻቱራንጋ» ተለውጦ «ቻትራንግ» ሆነ። ከዚህ ትንሽ በኋላ አረቦች ወረሩና ጨዋታውን ወድደው በቋንቋቸው ስሙን «ሻትራንጅ» አደረጉት። በኋለኛ ግሪክ ቋንቋ ደግሞ የሻትራንጅ ስም ወደ «ሳንትራዝ» ተለወጠ። «ሰንጠረዥ» የሚለው የአማርኛ ቃል ከዚህ ግሪክ ቃል እንደ ተነሣ ይመስላል።
በኢትዮጵያ ባህላዊ ሰንጠረዥ፣ ክፍል እስከሚማረክ ድረስ ተጫዋቾቹ እንደ ልባቸው (አለተራ) ይጫወታሉ። አለዚያ ጳጳሳትና ንግሥት ደካም በመሆናቸው እንደ ሻትራንጅ ይመስላል።
በዘመናዊ አውሮጳዊ ቼዝ (ከ1550 ዓ.ም. ጀምሮ) ጳጳስ እስከሚቻል ድረስ በሰያፍ ይጓዛል። ንግሥትም እስከሚቻል ድረስ በማንኛውም አግጣጫ ትሄዳለች። በተጨማሪ አንዴ ንጉስና ግንብ አንድላይ ሊዛወሩ የሚፈቅድና እንዲህ የሚመስል ልዩ ደንቦች አሉ። የ«ቼዝ» ስም ግን ከ«ቻቱራንጋ / ቻትራንግ» ሳይሆን ከፋርስኛ ቃል «ሳሕ-ማት» (የንጉሥ አደጋ) ተነሣ።
Seamless Wikipedia browsing. On steroids.
Every time you click a link to Wikipedia, Wiktionary or Wikiquote in your browser's search results, it will show the modern Wikiwand interface.
Wikiwand extension is a five stars, simple, with minimum permission required to keep your browsing private, safe and transparent.