መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ
From Wikipedia, the free encyclopedia
የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሕንፃ የመሠረት ድንጋይ ታኅሣሥ ፲፭ ቀን ፲፱፻፳፬ ዓ/ም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሲያስቀምጡ የእስክንድርያ ኮፕት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ዮሐንስ እና የሀገር ጳጳሳትም በተገኙበት ልዩ ጸሎት እና ቡራኬ ተሠጥቶ ተመረቀ። ቤተ ክርስቲያኑ ሲታነጽ ቀዳሚ ዓላማው ለአገራቸው ነፃነት ሲታገሉ ለተሰው አርበኞች መካነ መቃብር እንዲሆን ታቅዶ ነው።
የደብሩም ስም የሚያመላክተው ይኼንኑ እንደሆነ ነው። ታላቁ ምሁር ዓለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መንበር የሚለውን ቃል በቁሙ ወንበር፣ ግርንቡድ፣ መኖሪያ፣ ማረፊያ፣ መቀመጫ፣ ዙፋን፣ አትሮንስ፣ ድንክ፣ እረፍት፣ መደብ፣ ለመቀመጫ የተለየ ከፍ ያለ ቦታ እንደሆነ ሲገልጹ፤ ጸባኦት ደግሞ ሰራዊት፣ ጭፍራ፤ የጦር ሕዝብ፤ ብዙ ወታደር፤ ያርበኛ ጉባኤ፤ የዠግና ማኅበር እንደሆነ ያብራራሉ።[1]