አማኑኤል ካንት
From Wikipedia, the free encyclopedia
አማኑኤል ካንት ( Immanuel Kant) ከ(1724-1804) የነበረ ጀርመናዊ ፈላስፋ ሲሆን በምስራቃዊ ፕሩሲያ፣ ኮይንበርግ ከተማ ተወልዶ፣ ከዕለተ ውልደቱ እስከ እለት ሞቱ ከኮይንበርግ 50 ማልይ በላይ ሳይሄድ በዛች በትወሰነች ከተማ ኑሮውን መርቷል። ካንት በርግጥ ውጫዊ ህይወቱ ብዙ ለውጥ ያልታየበት ቢሆንም፣ በአስትሳሰብ ግን የዘመኑን ፍልስፍና ከስር-መሰረቱ ቀይሯል። "ቀኝ" እና "ግራ" በኅዋ ውስጥ እንዴት ሊለዩ ይችላሉ የሚለውን ጽሁፍ በ1770 ለዶክትሬቱ መመረቂያ ካቀረበ ጀምሮ ለዘመናዊ ፍልስፍና ያለመታከት ብዙ ጽሁፎችን አቅርቧል። በነዚህ ጽሁፎች ውስጥ የካንት መሪ ሃሳብ "ማንኛውም የሰው ልጅ እውቀት ከበስተጀርባው የሰው ልጅን አእምሮ በተነሳሽ (active) ተሳታፊነት ያጠይቃል" የሚል ሲሆን፣ በርግጥ ይህ አስተሳሰብ ቀላል መስሎ ቢታይም ውስጡ ግን ብዙ ከባድና የተወሳሰቡ ጽንሰ ሃሳቦችን በመያዙ ከሱ በኋላ ለተነሱ ፈላስፋወች የሃሳብ ውቅያኖስ በመሆን እስካሁን ዘመን ድረስ በሱ ስራ ላይ ጥናት ይካሄዳል።